በመንገድ ደህንነት ላይ የሚሰሩ አለም አቀፍ ተቋማት እና ባለድርሻ አካላት በመዲናዋ የፍጥነት አስተዳደር እና ቁጥጥር ላይ የመስክ ምልከታ አደረጉ
*************
(ት/ማ/ባ ሰኔ 3/2018 ዓ.ም) ፡- የአዲስ አበባ ትራፊክ ማጅመንት ባለሰልጣን በከተማዋ በፍጥነት አስተዳደርና ቁጥጥር የሚያከናውናቸውን ተግባራትን የመንገድ ደህንነት አለም አቀፍ ተቋማት የዘርፉ ቡድን አባላትና ባለድርሻ አካላት የመስክ ምልከታ አድርገዋል፡፡
የብሉምበርግ ኢኒሸቲቭ ፎር ግሎባል ሮድ ሴፍቲ ከፍተኛ አመራር ኬሊ ላርሰን፣ አለም አቀፍ የመንገድ ደህንነት ተቋማት፣የፊደራልና የክልል እንድሁም የልማት ድርጅቶችና የባለድርሻ አካላት ልኡካን ቡድኖች በከተማዋ በራዳር በታገዘዉ አዉቶማቲክ ኢንፎርስመንት ሲስተም የፍጥነት ቁጥጥርን የሲስተም አመዘጋገብ፣ የክፍያ ስርዓት፣ የቁጥጥር ቅንጅታዊ አሰራርና የቅሬታ ማቅረቢያ መንገዶች እና አፈታት ስርዓትን በመስክ ተመልክተዋል፡፡
ምልከታውን ያካሄዱት በመገናኛ አምቼ ወደ ቦሌ በሚወስደዉ መንገድ በጠዋትና ከሰዓት በነበረዉ የቁጥጥር ሂደት ከፍጥነት ወሰን በላይ ሲያሽከረክሩ የተገኙ ደንብ ተላላፊ አሽከርካሪዎች ላይ በአዉቶማቲክ ኢንፎርስመንት ሲስተም እንዴት ቁጥጥር እንደሚደረግ እና ለትራፊክ አደጋ ይበልጥ አጋላጭ በሆነዉ ከፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከር ላይ አሽከርካሪዎች ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸዉ ግንዛቤ በመስጠት ጎብኝዎቹ መልእክታቸዉን አስተላልፈዋል፡፡
የብሉምበርግ ኢኒሸቲቭ ፎር ግሎባል ሮድ ሴፍቲ ከፍተኛ አመራር ኬሊ ላርሰን በእዚሁ ወቅት እንደገለጹት አዲስ አበባ ከተማ የመንገድ ደህንነት ስራዎች ላይ ከ 30 ከተሞች አብሮ በመስራት ሂደት የተሻለ ለዉጥ በማምጣት በግንባር ቀደምትነት ትጠቃሳለች፡፡
ምልከታውም የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የብሉምበርግ ፊላንትሮፒስ ኢኒሽዬቲቭ ፎር ግሎባል ሮድ ሴፍቲ(BIGRS) ውጤታማነታቸው የተረጋገጡ የመንገድ ደህንነት ፖሊሲዎችን ለመተግበር ከመረጣቸው 13 ሀገራት እና ከ30 በላይ ክልሎች ውስጥ አንዱ በመሆኑ በቀጣይ በጋራ ለመስራት ከአዲስ አበባ ከተማ ተሞክሮ ለመዉሰድም ነው ብለዋል፡፡
ባለፈው ነሀሴ ወር የአዲ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን ባከናወነው የፍጥነት አስተዳደር አዲስ አበባ በዓይነቱ የመጀመርያ በሆነው እና ብሉምበርግ ኢኒሽዬቲቭ ፎር ግሎባል ሮድ ሴፍቲ ዋሽንገተን ዲስ ከተማ ላይ ባዘጋጀው ፍጥነትን ማሰተዳደር አለም አቀፍ ውድድር አዲስ አበባ ከተማ የወርቅ ሜዳልያ እና የመቶ ሺህ ዶላር ሽልማት ማግኘቷ ይታወሳል፡፡