ባለስልጣን መ/ቤቱ በካዛአንቺስ መልሶ ማልማት የኮሪደር ልማት ላይ በርካታ የምህንድስና ስራዎች ማከናወኑን አስታወቀ
• የመንገድ ቀለም ቅብ
• ምልክትና ማመላከቻ
• የመንገድ ትራፊክ መብራት ተከላ ይገኝበታል
*******************
(ት.ማ.ባ ሚያዝያ 20/2017 ዓ.ም):- የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን በከተማዋ በካዛአንቺስ መልሶ ማልማት የኮሪደር ልማት ላይ ያከናወናቸው የምህንድስና ተግባራት አለም አቀፍ የመንገድ ላይ የተሸከርካሪ እና እግረኛ መሻገሪያ ቀለም ቅብ፣ የትራፊክ ምልክትና ማመላከቻዎች እና የመንገድ ትራፊክ መብራት ተከላ ስራዎች እንደሆኑ አስታውቋል፡፡
ተግባራቱን በበላይነት እያከነወነ የሚገኘው በባለስልጣን መ/ቤቱ የመንገድ ደህንነት ምህንድስና ዳይሬክቶሬት ሲሆን ዳይሬክተሩ ኢ/ር መርጋ ሰፈራ እንደገለፁት እስከ አሁን በካዛአንቺስ መልሶ ማልማት አከባቢዎች 16,187 ሜትር የተቆራረጠ ነጭ ቀለም ቅብ፣ 17,388 ሜትር መንገድ አካፋይ ድፍን ቢጫ ቀለም ቅብ፣ 2,496.60 ሜትር ስኩዌር የእግረኞች ማቋረጫ /ዜብራ/፣ በቁጥር 52 ጠቋሚ ቀስቶች እና 337.59 ሜትር ስኩዌር ቢጫ ቼብሮን ቀለም ቅብ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡
እንዲሁም 7,745 ሜትር ድፍን ነጭ አካፋይ የብስክሌት መንገድ ቀለም ቅብ፣ 16,435.60 ሜትር ድፍን የጠርዝ ብጫ ቀለም ቅብ፣ 182.4 ሜትር ስኩዌር የብስክሌት መንገድ ላይ ዜብራ ማቋረጫ ቀለም ቅብ፣ 898.95 ስኩዌር ሜትር አረንጓዴ ቀለም ቅብ፣ እንዲሁም በቁጥር 71 የብስክሌት ምልክቶች እና 82 ጠቋሚ ቀስቶች ቀለም እንደተቀባ ኢ/ር መርጋ ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪ 498 የተሸከርካሪ ማቆሚያ /የፓርኪንግ/ ቦታዎች የ45 የአካል ጉዳተኞች ተሸከርካሪ ማቆሚያ ምልክቶች ጨምሮ፣ 4 ተርሚናሎች፣ አንድ የኤለክትሪክ መኪኖች ቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያ፣ ልዩ ልዩ ዓይነትና ይዘት ያላቸው የቀለም ቅብ ተግባራት እንደተከናወኑ አስረድተዋል፡፡
ኢ/ር መርጋ አያይዘውም በ6 መጋጠሚያ መንገዶች ላይ የመንገድ ትራፊክ መብራት ተከላ መከናወኑንና በዚህም 1,222 ሜትር መብራት መስመር ተዘርግቶ 21 ተንጠልጣይ ፖሎች እና 14 ቋሚ/መደበኛ/ ፖሎች ላይ 36 የትራፊክ መብራቶች ስራ ላይ መዋላቸውን ተናግረዋል፡፡
በመንገዶች፣ መጋጠሚያዎችና አደባባዮች ላይም 6 የአውቶቡስና ታክሲ መጫኛና ማውረጃ ምልክቶች፣ 12 የብስክሌት ምልክት፣ የፓርኪንግ አመላካች እና 1 ዝግ መንገድ በአጠቃላይ አለም አቀፍ የትራፊክ ምልክትና ማመላከቻዎች መተከላቸውን ኢ/ር መርጋ ገልጸው በመጨረሻም ቀን ከሌት ሰለቸኝ ደከመኝ ሳይሉ ስራው ላይ የተሳተፉትን የባለስልጣን መ/ቤቱ የበላይ አመራሮች፣ የክፍል ሃላፊዎችንና ባለሙያዎችን አመስግነዋል፡፡